1 Samuel 28

ሳኦልና የዓይንዶር ነዋሪዋ ሙታን ጠሪ

1በዚያን ዘመን ፍልስጥኤማውያን፣ እስራኤልን ለመውጋት ሰራዊታቸውን ሰበሰቡ። አንኩስም ዳዊትን፣ “አንተና ሰዎችህ አብራችሁኝ ለጦርነት መውጣት እንዳለባችሁ ዕወቁ” አለው።

2ዳዊትም፣ “አገልጋይህ ምን እንደሚያደርግ ያን ጊዜ አንተው ራስህ ታያለህ” አለው።

አንኩስም፣ “መልካም፤ በዘመኔ ሁሉ የራሴ የክብር ዘብ አደርግሃለሁ” ሲል መለሰለት።

3በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ሞቶ ነበር፤ እስራኤላውያንም ሁሉ በገዛ ከተማው በአርማቴም አልቅሰው ቀበሩት። ሳኦል ሙታን ሳቢዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ከምድሪቱ አባርሯቸው ነበር።

4ፍልስጥኤማውያን ተሰብስበው በመምጣት በሱነም ሲሰፍሩ፣ ሳኦል ደግሞ እስራኤላውያንን ሁሉ ሰብስቦ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ሰፈረ። 5ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ባየ ጊዜ ፈራ፤ ልቡም እጅግ ተሸበረ። 6እርሱም እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔር ግን በሕልምም ሆነ በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም። 7ሳኦልም አገልጋዮቹን፣ “እስቲ ሙታን ሳቢ ሴት ፈልጉልኝና ሄጄ ልጠይቃት” አላቸው።

እነርሱም፣ “እነሆ፤ ሙታን የምትስብ ሴት በዓይንዶር አለች” አሉት።

8ስለዚህ ሳኦል ሌላ ልብስ በመልበስ መልኩን ለውጦ ከሁለት ሰዎች ጋር በሌሊት ወደ ሴቲቱ ሄደ። እርሱም፣ “እባክሽ፣ መናፍስትን ጠይቂልኝ፤ የምነግርሽንም ሰው አስነሺልኝ” አላት።

9ሴትየዋ ግን፣ “እነሆ፤ ሳኦል ሙታን ሳቢዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ከምድሪቱ እንዴት እንዳጠፋና ያደረገባቸውን ታውቃለህ፤ ታዲያ፣ ታስገድለኝ ዘንድ በሕይወቴ ላይ ወጥመድ የዘረጋኸው ለምንድን ነው?” አለችው።

10ሳኦልም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ነገር ቅጣት አያገኝሽም” ሲል በእግዚአብሔር ስም ማለላት።

11ሴትዮዋም፣ “ማንን ላስነሣልህ?” ብላ ጠየቀችው።

እርሱም፣ “ሳሙኤልን አስነሺልኝ” አላት።

12ሴትዮዋም ሳሙኤልን ባየችው ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኸች፤ ሳኦልንም፣ “አንተ ሳኦል ሆነህ ሳለ፣ ለምን አታለልኸኝ?” አለችው።

13ንጉሡም፣ “አትፍሪ፤ ለመሆኑ ምን እያየሽ ነው?” አላት።

ሴትዮዋም፣ “አንድ መንፈስ
ወይም መናፍስት ወይም አማልክት
ከምድር ሲወጣ አያለሁ” አለችው።

14እርሱም፣ “መልኩ ምን ይመስላል?” ሲል ጠየቃት።

እርሷም፣ “ካባ የለበሰ አንድ ሽማግሌ ሰው እየወጣ ነው” አለችው።

ሳኦልም ሴትየዋ ያየችው ሳሙኤል መሆኑን ዐወቀ፤ በመሬትም ላይ ተደፍቶ እጅ ነሣ።

15ሳሙኤልም ሳኦልን፣ “አስነሥተህ የምታውከኝ ለምንድን ነው?” አለው።

ሳኦልም፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ፍልስጥኤማውያን እየወጉኝ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቋል፤ በነቢያትም ሆነ በሕልም አልመለሰልኝም፤ ስለዚህ ምን ማድረግ እንደሚገባኝ እንድትነግረኝ ጠራሁህ” አለው።

16ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “ታዲያ እግዚአብሔር ከራቀህ፣ ጠላትም ከሆነህ ለምን ትጠይቀኛለህ? 17እግዚአብሔር በእኔ የተናገረውን አድርጓል፤ እግዚአብሔር መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለጎረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል። 18ለእግዚአብሔር ስላልታዘዝህ፣ ታላቅ ቍጣውንም በአማሌቃውያን ላይ ስላልፈጸምህ እግዚአብሔር ዛሬ ይህን አድርጎብሃል። 19እግዚአብሔር አንተንና እስራኤልን ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ይሰጣል፤ አንተና ልጆችህም ነገ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር የእስራኤልን ሰራዊት ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ይሰጣል።”

20ሳሙኤል ከተናገረው ቃል የተነሣ፣ ሳኦል በፍርሀት ተውጦ ወዲያውኑ በቁመቱ ሙሉ መሬት ላይ ወደቀ፤ ቀኑንና ሌሊቱን ሁሉ እህል ስላልቀመሰ ጕልበቱ ዝሎ ነበር።

21ሴትየዋ ወደ ሳኦል መጥታ እጅግ መደንገጡን ባየች ጊዜ እንዲህ አለችው፤ “እነሆ፤ አገልጋይህ ቃልህን ሰምቻለሁ፤ በነፍሴም ቈርጬ የነገርኸኝን ፈጽሜአለሁ። 22አሁንም እባክህ አገልጋይህ የምትልህን ስማ፤ ብርታት አግኝተህ መሄድ እንድትችል፣ ጥቂት ምግብ ላቅርብልህና ብላ።”

23እርሱም፣ “አልበላም” በማለት እንቢ አለ።

ነገር ግን የራሱ ሰዎች ከሴትየዋ ጋር ሆነው አጥበቀው ስለ ለመኑት ቃላቸውን ሰማ፤ ከመሬትም ተነሥቶ በዐልጋ ላይ ተቀመጠ።

24ሴትዮዋም በቤቷ የሠባ ጥጃ ስለ ነበራት፣ ፈጥና ዐረደችው፤ ዱቄት ወስዳ ለወሰች፣ እርሾ የሌለው እንጀራም ጋገረች። 25ከዚያም ለሳኦልና ለሰዎቹ አቀረበችላቸው፤ እነርሱም በሉ፤ በዚያም ሌሊት ተነሥተው ሄዱ።

Copyright information for AmhNASV